ዓርብ 25 ጁላይ 2014

መላኩ ቅዱስ ገብርኤል በሐሙሌ 19 የሠራው ተዐምር

እንኮን ለሊቀ መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በዐል       በሰላም አደረሳችሁ

መላኩ ቅዱስ ገብርኤል #በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሐሙሌ 19 የሠራው ተዐምር ይሕ ነው

እለ እስክንድሮስ የተባለ መኰንን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑትን
ክርስቲኖች ለመቀጣትና ሌሎችም ፈርተው ክርስትናን
እንዳይፈልጉ ለማድረግ አስቦ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ፣
የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል አንድ ላይ
ተቀላቅሎ በብረት ጋን እንዲፈላ አዝዞ ነበር፡፡ ጭፍሮቹም
እለስክንድሮስ እንዳዘዛቸው ከአደረጉ በኋላ ያዘዝኸንን ሁሉ
ፈጽመን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፤ ድምፁ እንደነጐድጓድ ይጮሃል፤
ወላፈኑም እንደ ፀሐይ ነፀብራቅ በሩቅ ይጋረፋል፤ የፍላቱም
ኀይል አሥራ ዐራት ክንድ ያህል ከፍታ ወደላይ ይዘላል፤
እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ ሕፃን ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በክርስቶስ ስም
ስለሚያምኑ አሥረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ሊጨምሯቸው
ከእሥር ቤት አወጧቸው፡፡ ፍላቱ ወደ ላይ በሚዘል ብረት ጋን
ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው የእነዚህን ቅዱሳን
አሟሟት ያዩ ዘንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ
ታዘዘ፡፡
በዚህ ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማችና ባየች
ጊዜ ተሸበረች፤ ተዘጋጅቶላት ከነበረውም ክብር ልታፈገፍግ
ሞከረች፡፡
ልጅዋ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናት ሆይ ከዚህ የብረት ጋር
ግርማ የተነሣ አትፍሪ፤ ድንጋፄም አይደርብሽ፤ አናንያንና
አዛርያን፣ ሚሳኤልንም #እግዚአብሔር ከዕቶነ አሳት
እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን
ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ ፡፡ እናት ሆይ ከዚህ
ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለማዳን ስትይ
በማያልፈው በዘለዓለም እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሸን?
ይህስ አይሆንም፤ ይቅርብሽ፤ በአሁኑ ጊዜ #እግዚአብሔር
በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናቴ ሆይ ሶስናን ከእደ
ረበናት፣ /መምህራነ አይሁድ/ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ
እሱ እኛንም ከዚህ የጋን ፍላት ያወጣናል፡፡ ይልቁንም
#እግዚአብሔር በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም
ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን፣ ልጆቹንና ሚስቱን፣
በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባጣ ጊዜ እግዚአብሔርን
አመሰግነዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፤ #እግዚአብሔር ነሣ፤ /
ወሰደ/ #እግዚአብሔርም እንደ ወደደ አደረገ፤ ከማለት
በስተቀር ምንም የተናገረው ክፉ ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም
የሱን ዓላማ በመከተል ይህን መከራ ልንታገሥ ይገባናል፤
አላት፡፡
ነገር ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በዚህ ምክር ልትጽናና
ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ
አምላኬ ሆይ ይህችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ
ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለህ
ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን ይህን እንዳታደርግ ግን ቸርነትህ
ትከለክልሃለች፡፡
አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ አንድዱት፤ ቅጠሉን ግን
ጠብቁት፤ ብለህ ልታዝ መለኮታዊ ባሕርይህ አይደለም፤ ነገር
ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም ባንድ ጠብቁት፤ ብለህ ታዝዛለህ
እንጂ፤ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይህን ያየ ሁሉ ማዳን
የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከዚህ ከእሳት ባልሸሹም
ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡
አቤቱ ዲያብሎስም ከባለሥልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ፤
ቅዱሳኖቹንም ድል ነሣኋቸው፤ ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም
አንድ በግ ቀማሁ፤ በማለት እንዳይደነፋ ለናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ
መንፈስ ቅዱስን ስጣት፤ ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከኢየሉጣ
አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡
ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ በሰማያዊ መንግሥት አባት
የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታህ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን
ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ፤ እነሆ በብረት ጋኑ ውስጥ
የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም /በምንጭ/ ላይ
እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቼዋለሁና አለችው፡፡
እኒህም ቅዱሳን ይህን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን
የሚቆለምም፣ ልብን የሚያቀልጥ፣ ሆድን የሚሠነጥቅ፣
ሥርን የሚበጣጥስ መሣሪያ ካለበት የብረት ጋን ውስጥ
ጨመሯቸው፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ
ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፤ ከቅዱሳኑም
አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱ ጋን ማቃጠሉና
መፍላቱም ፀጥ አለ፡፡
ዳግመኛም እለ እስክንድሮስ ሀሳቡ ሳይሳካለት ስለቀረ አሥራ
አራት የሾሉና የጋሉ የብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን
በእናቱ በኢየሉጣ አካል፣ ሰባቱን በቂርቆስ አካል ይቸነክሯቸው
ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡
ዳግመኛም የሕፃንን የእራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ
ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህን
መከራ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው
በገመድ እንዲጎትቱት አዘዘ፤ በዚህም ጊዜ መልአኩ አዳነው፡፡
ሕዝቡም ይህን ሁሉ ተአምር በአዩ ጊዜ እግዚአብሔርን
አመሰገኑት፤ ቅዱስ ገብርኤልንም አከበሩት፡፡

ከበዐሉ ረድኤት በረከት ተካፋይ እንድንሆን አምላካችን ልውል #እግዚአብሔር ይርዳን

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ